ፀሐይ ባንክ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራረመ

ፀሐይ ባንክ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ግብርን በደራሽ ኤሌክትሮኒክ የክፍያ ስርዓት ለማከናወን የሚያስችለውን የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

 

ደራሽ የተቀናጀ የክፍያ ፕላትፎርም የግብር መጭበርበርን የሚቀንስ፣ የደንበኞችን እንግልት የሚያስቀር እና የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ 2025 ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡

 

የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፐሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ተቋሙ እስከ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ድረስ 53 በመቶ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በኤሌክትሮኒክ የክፍያ አማራጭ ክፍያዎቸን እየፈጸሙ እንደሚገኙ ገልጸው፤ በዚህ ሒደት ከሀገር ውስጥ ታክስ ብቻ 182 ቢሊዮን ብር በኤሌክትሮኒክ የክፍያ ስርዓት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

 

በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሀሚድ ደራሽ የተቀናጀ የክፍያ ፕላትፎርምን የሚጠቀሙ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥር እና የገንዘብ ዝውውር መጠን እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው፤ በፕላትፎርሙ አማካኝንት ከባንኮች ጋር በመቀናጀት 59 ቢሊዮን ብር እስከ የካቲት 18/2016 ዓ.ም. መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

 

ፀሐይ ባንክ በተመሰረተ አጭር ጊዜ ውስጥ ከ84 በላይ ቅርንጫፎች በመክፈትና ከ400 ሺህ በላይ ደንበኞችን በማፍራት የተሟላ፣ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት እየሠጠ እንደሚገኝ በስምምነቱ ላይ የተገኙት የፀሐይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና የባንኩ ቺፍ ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ወሰን አለምዬ አስታውቀዋል፡፡

ደህንነቱ የተረጋገጠውን ደራሽ የክፍያ ፕላትፎርም በመጠቀም የመንግሥት ገቢ በወቅቱ እንዲሰበሰብ ፀሐይ ባንክ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፤ ፀሐይ ባንክ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የገንዘብ ዝውውርና የግብር ክፍያ ሥርዓት ገቢራዊ ለማድረግ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል፡፡

 

በ2010 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው ደራሽ የተቀናጀ የክፍያ ስርዓት በአሁኑ ወቅት ከ21 ባንኮች ጋር ትስስር በመፍጠር እየሠራ ያለ ፕላትፎርም ነው።

 

ፀሐይ ባንክ
ለሁሉ!